አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በማስተላለፍ ኢትዮጵያ ከ13 ሚሊየን ዶላር በላይ እንድታጣ በማድረግ የተጠረጠረው ግለሰብ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክስ ቀረበበት።
ተከሳሹ ነጋሲ ተስፋልደት በ2017 ዓ.ም የወጣውን የባንክ ስራ አዋጅ ቁጥር 1360/2017 አንቀጽ 2 (6) (መ)፤ 3 (1) እና 90 (1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በመግለጽ ነው ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበው።
ተከሳሹ የባንክ ስራ ለመስራት ከብሄራዊ ባንክ የተሰጠ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው ለጊዜዉ ካልተያዙ ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ሲፈልጉ የሚላክላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር፣ የባንክ ሂሳብ ቁጥር እና የገንዘብ መጠን በሚያስተላልፉለት መረጃ መሰረት ገንዘቡን ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ የተለያዩ ግለሰቦች በስሙ ከከፈታቸው የባንክ ሂሳቦች ገንዘብ ማስተላለፉ በክሱ ተመላክቷል።
በአዋሽ ባንክ ተከሳሹ በስሙ በከፈተው የሂሳብ ቁጥር ከ2012 ዓ.ም እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ 578 ያህል ጊዜ 110 ሚሊየን 594 ሺህ 572 ብር ለተለያዩ ግለሰቦች አስተላልፏል ሲል ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ፤ ይህ ገንዘብ በህጋዊ አስተላፊዎች አማካኝነት ቢተላለፍ ሀገሪቱ 1 ሚሊየን 622 ሺህ ዶላር ታገኝ ነበር ብሏል።
እንዲሁም በአቢሲኒያ ባንክ በስሙ በከፈታቸው የሂሳብ ቁጥሮች ከሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሕዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 1 ሺህ 153 ጊዜ በአጠቃላይ 242 ሚሊየን 194 ሺህ ብር ለተለያዩ ግለሰቦች ገንዘብ አስተላልፎ በሕጋዊ አስተላላፊዎች በኩል ቢላክ ሀገሪቱ የምታገኘውን 3 ሚሊየን 469 ሺህ 923 ዶላር ማሳጣቱ በክሱ ተገልጿል።
እንዲሁም ተከሳሹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስሙ በከፈታቸው የሂሳብ ቁጥሮች በመጠቀም ከጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ሕዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 2 ሺህ 710 ጊዜ በአጠቃላይ 540 ሚሊየን 274 ሺህ ብር ለተለያዩ ግለሰቦች በማስተላለፍ በህጋዊ ገንዘብ አስተላላፊዎች አማካኝነት ቢላክ ሀገሪቱ የምታገኘውን 6 ሚሊየን 336 ሺህ 300 ዶላር ማሳጣቱን ዐቃቤ ሕግ አብራርቷል።
ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖረው በአጠቃላይ 1 ቢሊየን 1 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ለተላከላቸዉ ሰዎች በማስተላለፍ ገንዘቡ በህጋዊ ገንዘብ አስተላላፊዎች አማካኝት ወደ ሀገር ቢላክ ኖሮ ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረውን 13 ሚሊየን 31 ሺህ 200 የአሜሪካ ዶላር አሳጥቷል ያለው ዐቃቤ ሕግ፤ ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የባንክ ስራ በመስራት ወንጀል ግለሰቡ ላይ ክስ አቅርቧል።
በሲፈን መኮንን