የሀገር ውስጥ ዜና

2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዓመታትን ያስቆጠረ የሰው ልጅ ዝርያ በአፋር ክልል ተገኘ

By Adimasu Aragawu

January 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዓመታትን ያስቆጠረ እና ፓራንትሮፕስ የሚል ስያሜ ያለው የሰው ልጅ ዝርያ በአፋር ክልል ሚሌ ሎጊያ በተባለ ስፍራ ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር በሰጡት መግለጫ፥ ባለስልጣኑ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አንዱ የሰው ልጅ ቅሪት አካላት ላይ ምርምር ማድረግ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች ከውጭ ሀገራ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ባደረጉት ጥናትና ምርምር አትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነቷን በዓለም መድረክ አስተዋውቀዋል ነው ያሉት።

በዛሬው ዕለትም ከዚህ በፊት ያልታዬ የሰው ልጅ ዝርያ በአሜሪካ የችካጎ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ በሆኑት ዘረሰናይ ዓለምሰገድ (ፕ/ር) በተመራ ልዑክ መገኘቱን ተናግረዋል።

ግኝቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን እና ለአንተሮፖሎጂ ምርምር ኢትዮጵያ እና የአፋር ክልል ተመራጭ መሆናቸውን የበለጠ የሚያረጋግጥ መሆኑን አመላክተዋል።

ግኝቱ በዓለም ላይ ታዋቂ በሆነው ኔቸር መጽሔት ላይ በዛሬው ዕለት እንደሚታተም ጠቁመዋል።

በሚኪያስ አየለ