ቴክ

የፌዴራል ፖሊስን የሰው ሀብት አስተዳደር የሚያዘምኑ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች…

By Melaku Gedif

January 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ያበለጸጋቸው ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች ተመርቀዋል፡፡

የሰው ሃብት አስተዳደር (ኢአርፒ) ሥርዓቶቹ ተቋሙን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ከማድረግ ባለፈ የሀገሪቱን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ትልቅ እመርታ መሆናቸው ተመላክቷል።

ቴክኖሎጂዎቹ የሰው ሀብት አስተዳደርን፣ የሰራተኞች የራስ አገልግሎት መጠየቂያን፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የመታወቂያ ማተሚያን እና ዘመናዊ የሰነድ መዝገብ አስተዳደርን ያካተቱ ናቸው።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ÷ ዲጂታላይዜሽን ሥራን በኮምፒውተር ማከናወን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትንና ፍትሃዊነትን ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የራሳችንን የሀገር በቀል ዲጂታል መፍትሄዎች ማልማት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ያሉ ሲሆን÷ ይህ ስኬትም የውጭ ጥገኝነትን የሚያስቀር ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ÷ ቴክኖሎጂው በፖሊስ አገልግሎት ውስጥ የሚታዩ የመረጃ ክፍተቶችንና ማጭበርበሮችን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀር አመልክተዋል።

ሥርዓቱ በተለይ በፖሊስ ስም የሚፈጸሙ የሰነድ ቅጥፈቶችንና ማጭበርበሮችን በማስቀረት ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡

ቴክኖሎጂው የመረጃ ትንታኔ አቅምን በማሳደግ የወንጀል ምርመራ ስራዎች በሳይንሳዊ መረጃ ላይ ተመስርተው እንዲከናወኑና የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱም ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ያስችላልም ብለዋል።