አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና የምዘና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህር እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሥነ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ሳይንቲስት የሆኑት ጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) በዛሬው ዕለት ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ30 ዓመት በላይ ከማስተማር ባለፈ በዓለም አቀፍ የሥነ ምድር እና ከርሰ ምድር ውሃ ዘርፈ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
የከርሰ ምድር ውሃ ላይ ሰፊ እና ጥልቅ ምርምር በማካሄድ የሚታወቁ ሲሆን ÷ ከ2 ሺህ በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታተሙ የምርምር ሥራዎች ባለቤት ናቸው።
ለኢትዮጵያ በከርሰ ምድር የውሃ ዘርፍ ብዛት ያላቸው ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናታዊ ምርምሮችን በመስራት ቀዳሚ መሆናቸውንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ት/ት ክፍል የከርሰ ምድር ውሃ ተመራማሪ ሚካኤል ጥላሁን (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ባስተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎቻቸው እንደ አባት መካሪ ለሙያ ባልደረቦቻቸው ደግሞ እንደ ወንድም አጋዥ እንደነበሩም አውስተዋል፡፡
የበለስ ኢንጂነሪንግ መስራችና ባለቤት ጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነበሩ፡፡
የጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) ቀብር ሥነ ሥርዓት በነገው ዕለት ከቀኑ 9 ሰዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል የሚፈጸም ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጤናዓለም አየነው (ፕ/ር) ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና ተማሪዎቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል፡፡