አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ዘር አቅርቦት ስርዓትን በማጠናከር በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)።
ዋና ዳይሬክተሩ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ ኢንስቲትዩቱ በግብርና የዘር አቅርቦት ላይ ያሉትን ችግሮች ለመለየት የሚያስችል ጥናት አድርጓል፡፡
በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ የዘር ስርዓትን የሚያስተባብር የቴክኒክ ኮሚቴ መኖሩን ገልጸው፥ በኮሚቴው በተለያዩ ጊዜያት የሚከናወኑ ጥናቶች ለግብርና ሚኒስቴር እንደሚቀርቡ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሰረት በሚኒስቴሩ ይህንን ዘርፍ የሚያስተባብረው ስትሪንግ ኮሚቴ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በመንቀሳቀስ ችግሮች እንዲፈቱ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዋናነት መነሻ ዘር በማቅረብ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ዘርን በማባዛት አርሶ አደሩ ጋር ከማድረስ አንጻር የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጠንካራ የዘር አቅርቦት ስርዓትን እውን ለማድረግ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ