የሀገር ውስጥ ዜና

ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶቻችንን የሀገራዊ ሪፎርሙ አካል በማድረግ እየተሰራ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Hailemaryam Tegegn

January 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶቻችን ከዘመናዊ እሳቤዎችና አሰራሮች ጋር በማስተሣሠር የሀገራዊ ሪፎርሙ አካል በማድረግ እየተሰራ ነው አሉ፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለምአቀፍ ኮንፈረንስ “የሕግ የበላይነትና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች – ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘይቤዎች ለዕድገትና ለሰላም ግንባታ ከፍ ያለ ሚና አላቸው።

የክልሉ ሕዝብ በሺህ ዘመናት ታሪኩ ካካበታቸው ዕሴቶች አንዱ የፍርድ ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህ ባህላዊ የፍርድ ሥርዓቶች ባይኖሩ የፍትሕ ተቋሞቻችን በባለጉዳይ ብዛት ተጥለቅልቀው ሥራ ያቆሙ ነበር ነው ያሉት፡፡

ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ክርክሮች ተገማችነትና መረጋጋት እንዲሁም ፍትሕን በቅርበት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

በሀገራችን በተለያየ መንገድ የሚተገበሩት እነዚህ ሀገር በቀል አሠራሮችና ተቋማት በአነስተኛ ዋጋ እንዲሁም በአነስተኛ ጊዜና በተሻለ ቅቡልነት ፍትሕን ለማስፈን ዓይነተኛ መሣሪያ ሆነው ቆይተዋል ነው ያሉት።

የጎደላቸውን ሞልተን በትክክል ከተጠቀምንባቸው በጉዳዮች ብዛት በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙ መደበኛ የፍትሕ ተቋሞቻችንን ትርጉም ባለው ደረጃ ያግዛሉ ብለዋል።

በአማራ ክልል በተስተዋሉ የድህነት፣ የእኩልነት እጦት፣ ግጭቶች፣ ክርክሮችና የአለመግባባቶች መደራረብ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች መፈተናቸውን አንስተዋል፡፡

ባህላዊ መሠረቶቻችን ሳይሸረሸሩ ዘመናችን የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሠራሮች መጠቀም የሚችሉባቸውን ሁኔታ አብሮ ማጤን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የመደመር መንግሥት ከትናንት በጎ ዕሴቶችን መውሰድና ዛሬ አዳዲስ ዕሴቶችን መፍጠር ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ ያደርጋል ብሎ ያምናል ብለዋል፡፡

የነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ ከትናንት ያገኘናቸውን ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶቻችንን እና ዛሬ የገነባናቸውን መደበኛ የፍትሕ ሥርዓቶቻችንን አዎንታዊ ጥምረት ትፈልጋለች ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ሠረገላ ወደኋላ ላይመለስ እየበረረ በመሆኑ በጊዜ የሚሳፈሩት በጉዞው ውስጥ ሲካተቱ በጊዜ የማይሳፈሩት በረራውን መሬት ላይ ሆነው ይመለከታሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ፋታ የማይሰጠውን የብልጽግና ጉዞ ማቀላጠፍ የመላውን ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የጋራ ጥምረትና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኮንፈፍረንሱ በሁለት ቀናት ቆይታው ዘላቂ ሰላምን፣ የፍትህ ስርዓትንና ሀገር በቀል የፍትህ እሴቶችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው።

በለይኩን ዓለም