የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የፍትህ ሥርዓቱን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎች እየተሰሩ ነው

By Hailemaryam Tegegn

January 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የፍትህ ሥርዓቱን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎች እየተሰሩ ነው አሉ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው።

“የሕግ የበላይነትና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በባህርዳር ከተማ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

አቶ ዓለምአንተ በዚሁ ወቅት፥ የሕግ የበላይነት፣ ሰላምና ልማት የተሳሰሩ የሀገር ልማት አካላት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ፍርድ ቤቶች አለመግባባቶችን በመፍታት ለዘላቂ ሰላም፣ ፍትህ እና ልማት ሰፊ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ የዳኝነትና አጠቃላይ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፥ በዚህ ወቅት በክልሉ በዓመት እስከ 1 ሚሊየን የሚደርሱ አዳዲስ መዝገቦች እንደሚከፈቱ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ያለውን የፍትህ ስርዓት ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ዜጎች በግልጽ ፍትህ እንዲዳኙ ግልጽ የዳኝነት ስርዓት እንዲኖር ተሰርቷል ነው ያሉት።

ተገልጋዮች በያሉበት ሆነው የፍትህ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው የኤሌክትሮኒክስ መዝገብ ስርዓት መጀመሩን ጠቁመው፥ የርቀት ክርክር ወይም ስማርት ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ የባህል ፍርድ ቤቶችን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸው፥ ለአብነትም በባህርዳር ከተማ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ህንጻ ለመገንባት ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

የግልግል ዳኝነትን ተግባራዊ ማድረግ ከንግድና ኢንቨስትመንት የሚመነጩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡

በለይኩን ዓለም