የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ከኢትዮጵያውያን ውጪ ሌላ ማንም ሰው ግዴታ የለበትም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

January 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ጥቅም እና ፍላጎት ለማስከበር ከእኛ ኢትዮጵያውያን ውጪ ሌላ ማንም ሰው ግዴታ የለበትም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ የኢትዮጵያን ጥቅም፣ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማስከበር ከኛ ከኢትዮጵያውያን ውጪ ሌላ ማንም ሰው ግዴታ የለበትም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር የኢትዮጵያውያን ግዴታ፤ የወዳጆቻችን የፍቃድ ድጋፍ ይሆናል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያን ጥቅም እና ፍላጎት ማረጋገጥ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ስለሆነም ሃሳቡን በደንብ መገንዘብ እና በዚያው ልክ መተግበር እንደሚያስፈልግ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያስረዱት፡፡

የኢፌዲሪ አየር ኃይልን 90ኛ ዓመት በማስመልከት “የአንበሶቹ ሰማይ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርዒት በትናንትናው ዕለት በቢሾፍቱ ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷አየር ኃይላችን በብዙ ከፍታዎች ውስጥ ባለፈበት ወቅት ለሀገር ኩራትና መከታ ሆኖ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሞከሩ ሀይሎችን ማሳፈር የቻለ ታላቅ ተቋም ነው፡፡

እኛ ያለ ኢትዮጵያ እናት የለንም፤ ኢትዮጵያም ያለ እኛ ልጆች የሏትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ በተቸገረችበትና በደኸየችበት ጊዜ ወደ እንጀራ እናት የሄዱ ወገኖች የእንጀራ እናት ስለማታዛልቅ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡