የሀገር ውስጥ ዜና

ባንኮች ለተመረጡ የገቢ ዕቃዎች የጉምሩክ ዋጋን እንደ አመላካች ዋጋ ይጠቀማሉ – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

By abel neway

January 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባንኮች ለተመረጡ የገቢ ዕቃዎች ከጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የጉምሩክ ዋጋን እንደ አመላካች ዋጋ ይጠቀማሉ አለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ።

ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ ባንኮች ለተመረጡ የገቢ ዕቃዎች የብድር ሰነድ ይሁን ሌላ ክፍያ መንገድ ሲፈቅዱ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ተመንን እንደ አመላካች ዋጋ ሊጠቀሙ ይገባል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሐምሌ 2016 ዓ.ም ተግባራዊ ያደረገውን የውጭ ምንዛሪ መመሪያን ተከትሎ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉን አስታውሷል።

መመሪያው ባንኮች ከደንበኞቻቸው ጋር በመደራደር የውጭ ምንዛሪ መሸጫ እና መግዣ ተመኖችን መወሰን እንዲችሉ ይፈቅዳል ነው ያለው።

በተጨማሪም ባንኮች ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረው ዝቅተኛ የገቢ ዕቃዎች ዋጋ መመሪያ በመሰረዙ፤ አሁን ግን በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የገቢ የዕቃዎችን ዋጋ ትክክለኝነት የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሷል።

ይሁን እንጂ ባንኮች ለብድር ሰነድ የሚጠቀሙባቸው ዋጋዎች ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የማጣቀሻ ዋጋዎች ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው ባንኩ ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን አመልክቷል።

በመሆኑም የዋጋ ልዩነቶቹን ለማስተካከልና የዋጋ ማጣቀሻዎችን ለማጣጣም ሁሉም ባንኮች ከጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ተመንን እንደ አመላካች ዋጋ ይጠቀማሉ ነው ያለው።

ይህም በባንክ ሥርዓቱ እና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት ለማስወገድ እና የውጭ ምንዛሪ መረጃዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመላክታል፡፡