የሀገር ውስጥ ዜና

ድርድር ሲካሄድ መታሰብ ያለበት ለሀገር ያለው አበርክቶ ነው – ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር)

By Adimasu Aragawu

January 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ድርድር ሲካሄድ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ለሀገር ያለው አበርክቶ ነው አሉ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር)፡፡

የግድቡ ተደራዳሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረግ ድርድር ወቅት የሚነሱ ሃሳቦችን ከሀገር ዘላቂ ጥቅም ጋር በማመዛዘን መቀየስ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ወቅት የመጨረሻ ወለል የሆነ እና የማይታለፍ ቀይ መስመር ተቀምጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም በድርድሩ ወቅት ኢትዮጵያ የትኛውም አይነት ሃሳብ ቢነሳ ከዚህ በታች አልወርድም የምትልበት የመጨረሻ ወለል እንዲሁም ሰጥቶ መቀበል በድርድር የተለመደ አሰራር ቢሆንም መታለፍ የሌለበት የማይነካ መስመር አስቀምጣ ስትደራደር ነበር ብለዋል፡፡

የእኛ ቀደምቶች ያቆዩት የሀገር ጥቅም ዛሬ ላይ መልፈስፈስ እንደሌለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ስለሆነም የአሁኑ ትውልድ የወረሰውን ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ማሳመር እና ለቀጣይ ትውልድ አመቻችቶ ማቆየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ዛሬ የተበላሸ ጉዳይ በዘላቂነት መጥፎ ስለሚሆን ድርድር መቀየስ ያለበት ዘላቂ በሆነ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በብርሃኑ አበራ