አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጊፋታ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ የወላይታን ቱባ ባህልና ታሪክ ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ሚናው ጉልህ ነው አሉ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፡፡
የወላይታ ዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ “የጊፋታ ብስራቶች ለሕዝባችን ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት መሪዎች የተገኙበት መድረክ ተካሂዳል፡፡
አቶ ገብረመስቀል ጫላ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የጊፋታ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ የወላይታን ቱባ ባህል፣ ትውፊትና ታሪክ ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ሚናው ጉልህ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ከተሞች የተጀመረው ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የማጠናከርና አንድነትን ከፍ የማድረግ ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰላም፣ የመቻቻል እና የብልጽግና ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው÷ መንግሥት የሕዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች በየደረጃው ለመፍታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግብርና ሜካናይዜሽን እና የግብርና ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ትኩረት መደረጉንም ነው ያስረዱት፡፡
በማቴዎስ ፈለቀ