አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን የተቆጣጠረችበት መንገድ ድንገተኛ የበሽታ ሥርጭትን የመከላከል አቅሟን የሚያሳይ ነው አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ።
የኢትዮጵያ ድንገተኛ የማሕበረሰብ ጤና አደጋ ፈጣን ምላሽና አመራር ስኬቶች እንዲሁም የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ቁጥጥር ማብሰሪያ መድረክ ላይ ቫይረሱን መቆጣጠር መቻሉን ተከትሎ የእውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመከላከል የተገኘው ውጤት ትልቅ ትርጉም አለው።
ቫይረሱን ከኢትዮጵያ ማጥፋት የተቻለበት መንገድ የጤና ፖሊሲው ስኬት እንዲሁም የአመራር ቁርጠኝነትና ቅንጅት ማሳያ መሆኑን ገልጸው÷ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ የዜጎች ጤና ጥበቃ ስራ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ እየተሰራበት ነው ብለዋል።
ሳይንሳዊ አሰራርን በመከተል ፈጣንና የተቀናጀ ምላሽ የተሰጠበት ሥርዓት ኢትዮጵያን ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ መሆን እንዳስቻለ ያነሱት አፈ ጉባዔው÷ ይህም ኢትዮጵያ ለድንገተኛ በሽታ የማይበገር የጤና ሥርዓት መገንባቷን የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን የተቆጣጠረችበት መንገድ ድንገተኛ የበሽታ ሥርጭትን የመከላከል አቅም ማጎልበቷን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው÷ ቫይረሱን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት አስተዋጽዖ ያበረከቱት አካላትን አመስግነዋል።
አፈ ጉባዔው በቀጣይ የተገኘውን አስደናቂ ውጤት በማላቅ የጤና ሥርዓቱን አቅምና የማዘመን ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።