ቢዝነስ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ320 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ሰጠ

By Melaku Gedif

January 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር ለደንበኞች ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠሁ ነው አለ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ የገንዘብ ሚኒስትር እና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አሕመድ ሺዴ፣ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

አቶ አሕመድ ሺዴ በወቅቱ እንዳሉት ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል።

በተያዘው በጀት ዓመት የታቀደውን 10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ንግድ ባንክ ለፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፥ ይህንን በመረዳት ባንኩን ለማጠናከር በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፥ ደንበኛ ተኮር ሥርዓትን በመተግበር የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳለጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባንኩ ከ45 ሚሊየን በላይ ደንበኞች በማፍራት ከፍተኛ የቁጠባ ባህልን በማስፋፋት በርካቶች ጥሪት እንዲያፈሩ የበኩሉን ተወጥቷል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከ320 ቢሊየን ብር በላይ ብድር መሰጠቱን አመልክተዋል።

ባንኩ በመንፈቅ ዓመቱ ያልተጣራ 36 ነጥብ 19 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል።

በሥራ ሒደት የሚነሱ ቅሬታዎችን በፍጥነት የሚፈታ ግልጽ አሰራር መዘርጋት መቻሉንም ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 1 ነጥብ 69 ትሪሊየን ብር የደረሰ ሲሆን ÷ ጠቅላላ ሃብቱም 2 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር መሻገሩን አስታውሰዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም መጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ከ325 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ ያሰባሰበው ባንኩ÷ አጠቃላይ ተቀማጩን 2 ትሪሊየን ብር ማድረስ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመተግበር ከሚስተናገዱ ጠቅላላ ግብይቶች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በዲጂታል አማራጭ እንደሚከናወኑ ተመላክቷል፡፡

በመላኩ ገድፍ ፡-