አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በክልሉ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኩል ተገልጋዮችን በስፋት ለማስተናገድ ትኩረት ተሰጥቷል አለ።
በቢሮው መሶብ የአንድ ማዕክል አገልግሎት አስተባባሪ ተማረ አቤ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ ሶስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋቁሞ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል።
በባህርዳር ከተማ ሁለት፣ በደሴ ከተማ አንድ በአጠቃላይ ሶስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደተከፈተ ገልጸው፤ ማዕከላቱ ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በክልሉ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 10 የክልል እና አራት የፌዴራል ተጠሪ የሆኑ በአጠቃላይ 14 ተቋማትን ይዞ መደራጀቱን ተናግረዋል።
በዚህም ከ54 በላይ መንግስታዊ አገልግሎቶችን በመለየት፣ በማደራጀት እና ዲጂታላይዝ በማድረግ እንዲሁም ለሙያው ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን በማካተት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
አገልግሎቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት እንዲሰጥ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሁሉም የክልሉ ሪጆፖሊታን ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደሚጀምር አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም አገልግሎቱን በክልሉ በሚገኙ መካከለኛ ከተማ አስተዳደሮች ለማስጀመር ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በማዕከላቱ እስካሁን ከ26 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን 95 በመቶ የሚሆኑ ደንበኞች በአገልግሎቱ ደስተኛ መሆናቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ