አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጀመሩ ሰው ተኮር ሥራዎች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈጻጸም ግምገማ ላይ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም በየትኛውም ሁኔታ ሕዝብን በአግባቡ ማገልገል የሚችሉና ቀጣይነት ያላቸው ጠንካራ ተቋማትን የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
የገቢ አሰባሰብ ሒደትን ይበልጥ በማዘመን ከተማዋ የምታመነጨውን የገቢ አቅም በሚገባ ለመጠቀም በትኩረት እና በቅንጅት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
በግብይት ሥርዓቱ ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ እስፈላጊው ርምጃ አንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመኑን የዋጀ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
በተቋማት መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር መስራት ይገባል ያሉት ከንቲባዋ ÷ የጋራ አላማን ለማሳካት ትብብርና በቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሁሉም ዘርፎች፣ አመራሮችና ሰራተኞች መካከል ጤናማ ውድድር መፍጠር እንዲሁም አዳዲስ ሥራ ፈጠራዎችን ማበረታታት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የሚመጡ የሕዝብ ጥቆማዎችን በአግባቡ በመጠቀም ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በመለየትና በመከላከል አስፈላጊ ርምጃ መውሰድ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ማጠናከር፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን ማበረታታትና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በመዲናዋ የተጀመሩ አበረታች ሰው ተኮር ሥራዎችን ከዘላቂ ልማት ጋር በማስተሳሰር ተረጂነት መቀነስ እንደሚገባ አመልክተዋል ከንቲባዋ፡፡
በመዲናዋ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምቹ ምሕዳር መፍጠር ይገባል ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ በተለይም የሚነሱ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በተማሏ ውኔታ ምላሽ በመስጠት መሰረት መጣል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አመራሮች ሕገ ወጥነትን ከመከላከል ጎን ለጎን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት ሒደት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በታጋሽነትትና በብልሃት መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ ሥራዎች ላይ የሕዝብን ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት እና ግልጸኝነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ከንቲባ አዳነች አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-