ስፓርት

በማንቼስተር ሲቲ አጀማመሩ የሰመረለት አንቶኒዮ ሴሜንዮ…

By Melaku Gedif

January 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፕሪሚየር ሊጉ በቦርንማውዝ በመድመቅ ደረጃውን ከፍ አድርጎ ወደ ኢትሃድ ያቀናው አንቶኒዮ ሴሜንዮ በማንቼስተር ሲቲ ቤት በፍጥነት መላመድ ችሏል፡፡

ከጋናዊ አባቱ እና ፈረንሳዊ እናቱ በፈረንጆቹ 2000 በእንግሊዝ የተወለደው ሴሜንዮ በሊጉ ደማቅ አንቅስቃሴን እያደረጉ ከሚገኙ የፊት መስመር ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

ሴሜንዮ በልጅነቱ በአርሰናል፣ ቶተንሃም ሆትስፐር እና ሚልዎል እግር ኳስ ክለቦች ያልተሳካ ሙከራ ያደረገ ሲሆን÷ በ15 ዓመቱ በክሪስታል ፓላስም አትችልም ተብሎ መባረሩ ይታወሳል፡፡

ከብዙ ውጣ ውረዶች እና ተስፋ መቁረጥ በኋላ በ2017 የሻምፒዮን ሺፑን ቡድን ብሪስቶል ሲቲ አካዳሚን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በክለቡ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል፡፡

በብሪስቶል ሲቲ ባሳየው ድንቅ ብቃት የፕሪሚየር ሊጉን ቡድን ቦርንማውዝን በፈረንጆቹ 2023 በ10 ሚሊየን ፓውንድ እንዲቀላቀል አስችሎታል፡፡

በስፔናዊው አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ በሚመራው ቦርንማውዝ ተጽዕኖን በጉልህ ማሳረፍ የቻለው ሴሜንዮ÷ ማንቼስተር ሲቲን በጥር የተጫዋች የዝውውር መስኮት በ64 ሚሊየን ፓውንድ መቀላቀሉ ይታወቃል፡፡

በፈጣን እንቅስቃሴው፣ በሁለቱም እግሮቹ በምቾት መጫወት መቻሉ እና በግብ አስቆጣሪነቱ በልዩነት የሚታወቀው ተጫዋቹ የማንቼስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ተስፋ ያለመልማል ተብሎ በስፋት ተገምቷል፡፡

በማንቼስተር ሲቲ አጀማመሩ ያማረለት ሴሜንዮ ለክለቡ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር በሚያደርገው የዋንጫ ፉክክር የሴሜንዮ መቀላቀል በሚታይ መልኩ ለውጥ እያመጣ ይገኛል፡፡

መነሻው ትንሽ የነበረው ሴሜንዮ መዳረሻው ማንቼስተር ሲቲ ከመሆኑም ባለፈ የቡድኑ የቁርጥ ቀን ልጅ ይሆን ዘንድ በውሃ ሰማያዊዎቹ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ምንም እንኳን በእንግሊዝ ቢወለድም ለአባቱ ሀገር ጋና መጫወትን ምርጫ ያደረገው የ26 ዓመቱ አንቶኒዮ ሴሜኒዮ የጋና ብሔራዊ ቡድን የቀጣዩ ዘመን የስኬት ምንጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአቤል ነዋይ