የሀገር ውስጥ ዜና

ከ1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጓዘ

By Yonas Getnet

January 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 6 ወራት ከ1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል አለ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የ2018 በጀት ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መድረኩ የሥራ አፈጻጸምን በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ለማሻሻል ያለመ ነው፡፡

በግማሽ ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመው ÷ በዚህም የገቢ ዕቅዱን 113 ከመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በመንፈቅ ዓመቱ 800 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ታቅዶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይም ከ1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ማጓጓዝ መቻሉን ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡

በቅድስት አባተ