የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ዝግጅት

By Mikias Ayele

January 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፎ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራ በማከናወን ላይ እንገኛለን አሉ፡፡

ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አልማዝ ገ/ፃዲቅ÷ በትግራይ ክልል 17 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊ እውቅና አግኝተው መመስረታቸውን አንስተዋል፡፡

ይህም የክልሉ ወጣቶች እና ህዝቡ አዲስ አስተሳስብ እና አዲስ የፖለቲካ አመለካከት እንደሚፈልግ ከፍተኛ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ስምረት ለእነዚህን አዳዲስ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት መቋቋሙን ጠቅሰው÷ የእጩ ምልመላን ጨምሮ ፓርቲው ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ህዝብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና እንዲያገኝ ምርጫ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው÷ ህዝቡ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል።

የሹም ተምቤን ፓርቲ ሊቀመንበር ጎይቶም ወ/ማሪያም በበኩላቸው÷ በክልሉ አሳታፊ ምርጫ ባለመኖሩ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲፈጠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በክልሉ ሁሉም ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው አማራጭ ሀሳባቸውን እና የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን እንዲያስተዋውቁ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ፓርቲያቸው በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች በምርጫው እንደሚፎካከር ገልጸው፤ ለዚህም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹ ለምርጫው ስኬታማነትም የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

በሚኪያስ አየለ