ቢዝነስ

የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት 106 ቢሊየን ብር ደረሰ

By Yonas Getnet

January 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ መንፈቅ የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት 106 ቢሊየን ብር መድረሱን ባንኩ አስታወቀ።

የዘመን ባንክ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት የባንኩ የስድስት ወራት እንቅስቃሴ ውይይት መድረክ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ዘበነ እንዳሉት፤ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት 106 ቢሊየን ብር ደርሷል።

የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ደግሞ 80 ቢሊየን ብር ደርሷል ብለዋል።

ይህም ባንኩ የተረጋጋ ዕድገትና ጠንካራ የደንበኞች አመኔታ እንዳለው የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፤ በስድስት ወሩ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ መመዝገቡን እና የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 14 ቢሊየን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ካለፈው በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው የላቀና ስኬታማ የሥራ ጊዜ ማሳለፍ የተቻለበት እንደነበር አመልክተዋል።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ እንዬ ቢምር በበኩላቸው፤ በሁለተኛው አጋማሽ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማግኘት ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዘመን ባንክ ጠንካራ ደንበኛ ተኮር የባንክ አገልግሎት፣ በጥንቃቄ የሚመራ የፋይናንስ አስተዳደር እና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑ ተገልጿል።