አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በታዳሽ እና ዘላቂ የኢነርጂ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
በ27ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሞቃዲሾ ያቀኑት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከአውሮፓ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሜሪያም ፌራን ጋር ተወያይተዋል።
በወይይቱ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ የአውሮፓ ህብረት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለታዳሽ፣ የተቀናጀ እና ዘላቂ ኢነርጂ መርሐ ግብር የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
ሜሪያም ፌራን በበኩላቸው÷ ተቋማቸው የምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ አካል የሆነውን የኢትዮ ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር በፋይናንስ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራሞች እንዲደግፍ ከስምምነት ላይ መደረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡