አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አጠቃላይ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ነው አለ።
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ጌትነት ስሜ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
በዚህም በገጠርም ሆነ በከተማ የህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 1 ሚሊየን 636 ሺህ 309 የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መደረጉን ገልጸው፤ 79 ሚሊየን 592 ሺህ 322 የነበረውን አጠቃላይ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ህዝብ ወደ 81 ሚሊየን 240 ሺህ ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።
በተለይም ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን አንስተው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ድርቅ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸው አራት ወረዳዎች አጠቃላይ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሊሆኑ መቻላቸውን ገልጸዋል።
1 ሺህ 370 የገጠርና የከተማ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ እና ማስፊፊያ ተካሂዷል ያሉት አቶ ጌትነት፤ የውሃ ተቋማት ብዛት የተካሄደባቸው ብዛት 231 ሺህ 540 መድረሱን ጠቁመዋል።
በአቢይ ጌታሁን