አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ከ85 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የ2018 በጀት ግማሽ ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ኢትዮ ቴሌኮም ጥራቱን የጠበቀ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የገቢ ምንጭን በማስፋት እና የደንበኞችን ቁጥር እንዲሁም እርካታ ከማሳደግ አንጻር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በግማሽ ዓመቱ ከ85 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ÷ በዚህም የእቅዱን 81 በመቶ ማሳካት መቻሉን አብራርተዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ ደንበኞች ቁጥር 87 ነጥብ 1 ሚሊየን መድረሱን ጠቁመው፥ ከባለፈው ዓመት በ6 ሚሊየን ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት።
በግማሽ ዓመቱ 133 ከተሞች የ4ጂ ኔትወርክ ተጠቃሚ መሆናቸውንና አሁን ላይ 4ጂ ኔትወርክ ተጠቃሚ ከተሞች 1 ሺህ 69 መድረሳቸውን አመልክተዋል።
278 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች መገንባታቸውን ጠቅሰው፥ አጠቃላይ ሞባይል ጣቢያዎች ቁጥርም 10 ሺህ 288 ደርሷል ብለዋል።
በዚህም በተለይም በገጠር አካባቢ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኔትወርቅ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የተለያዩ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን መተግበር መቻሉን አስገንዝበዋል።
204 ምርትና አገልግሎቶች ለደንበኞች የቀረቡ ሲሆን÷ ከእነዚህም 81ዱ አዳዲስ፤ 74 የሚሆኑት ደግሞ ማሻሻያ የተደረገባቸው እንደሆኑ ተመላክቷል።
በመላኩ ገድፍ