ቴክ

በቴክኖሎጂ ዘመኑን የዋጀ ትውልድ ለመፍጠር…

By Yonas Getnet

January 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቴክኖሎጂ ዘመኑን የዋጀ ትውልድ ለመፍጠር የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ።

የቢሮው ኃላፊ መለሰ በየነ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ በቴክኖሎጂ ዘመኑን የዋጀ ትውልድ ለመፍጠር እንደ ሀገር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

በክልሉም ኢኒሼቲቩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የክልሉን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስልጠናው ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ የትምህርት፣ ጸጥታ እና ሌሎች ተቋማት ላይ ስልጠናውን የመስጠት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው÷ አመራሩ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የስልጠናው ተሳታፊ እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዚህም በ2018 በጀት ዓመት ከ25 ሺህ 400 በላይ ዜጎች ስልጠናውን እንዲወስዱ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን ከ13 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠና ማግኘቱን አመልክተዋል።

ከ7 ሺህ 400 በላይ ሰልጣኞችም ስልጠናውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ሀገሪቱ የያዘቸውን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻዎች ርብርብ እንዲያደርግና ወጣቱ ትውልድም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን አቶ መለሰ ጥሪ አቅርበዋል።

በዮናስ ጌትነት