ቢዝነስ

760 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

By Yonas Getnet

January 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በተያዘው በጀት ዓመት 760 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል አለ።

ሚኒስቴሩ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ከሌሎች ሀገራት ጋር ተመሳሳይ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እንዲኖር ለማስቻል የገቢ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ስራ ተገብቷል።

በዘርፉ የተደረገው የሪፎርም ስራም ውጤት ማስገኘት መጀመሩን ጠቅሰው÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት 640 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 709 ቢሊየን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ አመልክተዋል።

በዚህም ከዕቅዱ አንጻር ከ110 በመቶ በላይ መሳካቱን አንስተው÷ የጥር ወር ሲጨመር 760 ቢሊየን ብር እስካሁን መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥም የሀገር ውስጥ 366 ቢሊየን ብር እንዲሁም ከቀረጥና ታክስ 342 ቢሊየን ብር ድርሻ እንዳላቸው አብራርተዋል።

ለተመዘገበው የተሻለ አፈፃፀም ግብር ከፋዮችን፣ አስመጪና ላኪዎችን እንዲሁም የገቢ ዘርፍ ሰራተኞችን አመስግነዋል።

በዳዊት ጎሳዬ