የሀገር ውስጥ ዜና

በህገወጥ የባንክ ሥራ ኢትዮጵያ ከ14 ሚሊየን ዶላር በላይ እንድታጣ በማድረግ የተጠረጠረችው ቻይናዊት ግለሰብ ክስ ተመሰረተባት

By sosina alemayehu

January 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ውጪ የባንክ ሥራ በመስራት ኢትዮጵያ ከ14 ሚሊየን ዶላር በላይ እንድታጣ በማድረግ የተጠረጠረችው ቻይናዊት ግለሰብ ክስ ተመሰረተባት፡፡

ሊንግ ቹንግ የተባለችው ተከሳሽ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚገኙ ሰዎች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ሲፈልጉ በእነዚያ ሀገራት ከሚገኙ ያልተያዙ ግብረ አበሮቿ ጋር ገንዘቡን በመሰብሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ 10 ግለሰቦች ሲያስተላልፉ መቆየታቸው በክሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

ተከሳሿ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፈተችው የሂሳብ ቁጥር በመጠቀም ከሕዳር 30/2013 ዓ.ም እስከ ሕዳር 4/2018 ዓ.ም 1ሺህ 112 ጊዜ በአጠቃላይ ብር 636 ሚሊየን 157 ሺህ ብር ለተለያዩ ግለሰቦች ማስተላለፋቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ይህ ህገወጥ የባንክ ስራ ገንዘቡ በህጋዊ የገንዘብ አስተላላፊዎች በኩል ቢተላለፍ ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረውን 10 ሚሊየን 492 ሺህ ዶላር አሳጥቷታል ብሏል፡፡

በተጨማሪም በአቢሲኒያ ባንክ በስሟ በከፈተችው የሂሳብ ቁጥር በመጠቀም ከሕዳር 10/ 2014 ዓ.ም እስከ ሕዳር 04/2018 ዓ.ም ድረስ ከ201 ጊዜያት በላይ በድምሩ 233 ሚሊየን 433 ሺህ ብር ለተለያዩ ግለሰቦች ማስተላለፏን ክሱ አመላክቷል፡፡

ይህ ገንዘብ በባንኮች ወይም በህጋዊ መንገድ ቢላክ ኖሮ ሀገሪቱ ታገኝ የነበረውን 4 ሚሊየን 37 ሺህ ዶላር ማሳጣቷንም ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡

ግለሰቧ ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ለተላከላቸው ሰዎች በአጠቃላይ ከ839 ነጥብ 59 ሚሊየን ብር በላይ በህገወጥ መንገድ በማስተላለፍ ኢትዮጵያ ልታገኝ የነበረውን ከ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ በማድረግ ተጠርጥራ ክስ ተመስርቶባታል፡፡

የክስ መዝገቡን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ሲሆን፥ ግለሰቧ ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ውጪ የባንክ ስራ በመስራት ወንጀል ክስ ተመስርቶባታል፡፡

በዚህም በ2017 ዓ.ም የወጣውን የባንክ ስራ አዋጅ ቁጥር 1360/2017 አንቀጽ 2 (6) መ እንዲሁም አንቀጽ 90 (1) ስር የተመላከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽማለች ሲል ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

በመቅደስ ከበደ