የሀገር ውስጥ ዜና

ለመሪዎች ጉባኤ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል – አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ

By Hailemaryam Tegegn

January 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቅርቡ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ የትራንስፖርት፣ የሆቴል ዝግጅትና የደህንነት ስራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በጉባኤው በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሌሎችም መስኮች ለመወያየት ትኩረት ሊደረግባቸው በታቀዱ ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ ከህብረቱና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በሰፊው እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ትልልቅ የልማት ስራዎችን ለመጎብኘት ከተለያዩ ሀገራት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ እንዲሁም በኮሪደር ልማትና በሌሎች መስኮች የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ በተጠናከረ መልኩ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ እንግዶችን ተቀብሎ በተሟላ ሁኔታ ለማስተናገድ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን በአህጉራዊ መድረኮች ያላትን ሚና ለማጠናከርና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

ለዚህም የሀገራችንን ትልቅነት፣ ክብርና አኗኗር ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ ለጉባኤው ስኬት የሁሉም አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ መልእክት አስተላልፈዋል።

በቅድስት ዘውዱ