አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታዋቂው ሼፍ ማርከስ ሳሙኤልሰን የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለዓለም እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡
ሼፍ ማርከስ “ኢተር” ከተባለው ዓለም አቀፍ የምግብ እና ባህል መፅሔት ጋር ባደረገው ቆይታ÷ ሬስቶራንቶች እና የኪነ ጥበብ ተቋማት ለአዲስ አበባ አዲስ መልክ እየሰጡ እንደሚገኙ አንስቷል፡፡
በተጨማሪም ሙዚየሞች፣ የኤግዚቢሽን ማዕከላት፣ የገበያ አዳራሾች እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ለከተማዋ ድምቀት እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት የተከፈተው እና ራሱ የሚያስተዳድረው “ማርከስ አዲስ ሬስቶራንት እና ስካይ ባር” የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ለዓለም አቀፍ እንግዶች በማቅረብ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ አብራርቷል፡፡
ሬስቶራንቱ ከአሰራር ዲዛይኑ ጀምሮ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች በዘመናዊ መንገድ በማቅረብ ምግቦቹ ከኢትዮጵያውያን ውጭ በሌሎች ሀገራት እንዲለመዱ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚበቅለው ጤፍ የሚዘጋጀው የጤፍ ፓስታ በሬስቶራንቱ ብቻ እንደሚዘጋጅ በመጥቀስ፣ የዶሮ ወጥ፣ ቃተኛ፣ ክትፎ፣ ጥሬ ስጋ፣ በየአይነት፣ ሽሮ እና ሌሎች በርካታ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በሬስቶራንቱ እንደሚዘጋጁ ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም ሬስቶራንቱ ከተለያዩ የምግብ ማሰልጠኛዎች እና ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ለወጣቶች የምግብ ዝግጅት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል ብሏል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የምግብ እና ሆቴል አገልግሎት እንዲስፋፋ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ነው ያስገነዘበው፡፡
የምግብ ባለሙያዎችን በማስልጠን በራሱ ሬስቶራንት ተቀጥረው እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል።
በቀጣይ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች ከሀገር ውጭ እንዲተዋወቁ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ሼፍ ማርከስ ተናግሯል፡፡
በሚኪያስ አየለ