አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣይ ወር ለሚካሄደው 39ኛ የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባኤ ሆቴሎች እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል አለ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማሕበር፡፡
የማሕበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ብሌን መላኩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ ሆቴሎች ከቀደመው ጊዜ በበለጠ እንግዶችን ለመቀበል እና የተሻለ መስተንግዶ ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡
ማሕበሩ እንግዶች የሚፈልጉትን ማንኛውንም አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ሆቴሎች አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት።
አስተማማኝ የደኅንነት እንዲሁም ጥራት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት ከቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻዎች ጋር ሰፊ ስራዎች መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡
በመዲናዋ ስብሰባውን ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች የሀገሪቱን ባህል እና እሴት በጠበቀ መልክ መስተንግዶ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ ሂደት ለቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎች ስልጠና መሰጠቱንና በቂ ዝግጅት መደረጉንም ምክትል ፕሬዚዳንቷ አብራርተዋል፡፡
ሆቴሎች የሀገራቸውን የሕዝብ ግንኙነት ስራን በአግባቡ መስራት እንዲችሉ ከቋንቋ ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡