የሀገር ውስጥ ዜና

የባካሪ ሳኛ ጉብኝት ለስፖርት ቱሪዝም ሚናው ከፍተኛ ነው – ሰላማዊት ካሳ

By Mikias Ayele

January 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርሰናል የቀድሞ ተከላካይ ባካሪ ሳኛ በኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝት ለስፖርት ቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል አሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፡፡

ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ከሚገኘው ባካሪ ሳኛ ጋር ተገናኝተው የኢትዮጵያ ቆይታውን በተመለከተ ተወያይተዋል።

በውይይቱ በአዲስ አበባ በየአካባቢው የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አንስተናል ብለዋል፡፡

ባካሪ ሳኛ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና የአንድነት ፓርክን ጨምሮ ልዩ ልዩ ስፍራዎችን መጎብኘቱን ጠቅሰው፤ በከተማዋ የተመለከታቸው መዳረሻዎች ቀደም ሲል ስለ ኢትዮጵያ የነበረውን አመለካከት እንደቀየሩለት መመስከሩን ተናግረዋል።

በተለይም ስፖርት ወዳድ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ያደረጉለት የሞቀ አቀባበል እንዳስደሰተው መግለጹን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

እንደ ባካሪ ሳኛ አይነት ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ኮኮቦች ወደ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ መሳብ ለስፖርት ቱሪዝም ያለው ሚና ከፍተኛ ነው በማለት ሚኒስትሯ አብራርተዋል።