ቢዝነስ

የቁም እንስሳት ንግድ ሥርዓትን በማዘመን የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ…

By Mikias Ayele

January 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የቁም እንስሳት ንግድ ሥርዓትን በማዘመን የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው አሉ።

ሚኒስትሩ በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ ቀይ አፈር ከተማ ‘የቀይ አፈር 2ኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል’ ግንባታን አስጀምረዋል።

ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ግንባታው የገበያ መሠረተ ልማት ስብራትን ለመጠገን እና የንግድ ሥነ-ምህዳሩን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ለማዘመን የተጀመረው ስትራቴጂካዊ ጉዞ አካል ነው።

የቁም እንስሳት ንግድ ሥርዓቱን ማዘመን አርብቶ አደሩ ከምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ እና የሀገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ እንዲያድግ ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የቀይ አፈር 2ኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል ግንባታ ወጪ የሚሸፈነው በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በ’ድራይቭ ፕሮጀክት’ መሆኑ ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ በሞያሌ ቢቃ መሰል ግንባታ የጀመረ ሲሆን፤ በደገሀቡር፣ በሰመራ እና በኤልብኮ የሚገኙ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

በመላኩ ገድፍ