አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባለፉት ሰባት ዓመታት በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ያከናወናቸው የሪፎርም ትግበራ ሥራዎች ውጤታማ ነበሩ አሉ።
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘውን የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ያስገነባውን አዲስ ህንጻ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የአገልግሎቱ አመራሮች ገለጻ ማድረጋቸውን አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ አስታውቋል።
አገልግሎቱ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ባካሄዳቸው ሥር ነቀልና ተከታታይ ተቋማዊ የሪፎርም ትግበራዎች በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል፣ አሠራርና አደረጃጀት አስደናቂ እመርታዎች የተመዘገቡ መሆናቸውን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) የተለያዩ ሀገራት አቪየሽን ደኅንነት የሥራ እንቅስቃሴዎችን የማየትና የመታዘብ እድል እንደገጠማቸው ገልጸው፤ በኢትዮጵያ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ለአፍሪካ ተምሳሌት ይሆናል ብለዋል።
በአገልግሎቱ ሥር የሚገኘው የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፉ የታጠቃቸው ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነትና ተወደዳሪነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መሃዲ (ዶ/ር) ናቸው።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሀገሪቱ የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በማድረግ በኩል ከፍተኛ የአመራር ክትትል፣ ቁጥጥርና ቁርጠኝነት የተስተዋለ እንደነበር መግለጻቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል።