አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው መዋኛ ገንዳ በፊፋ ስታንዳርድ የተገነባ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል ነው አለ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን።
የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሽመልስ ደፋር እንዳሉት÷ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው መዋኛ ገንዳ በፊፋ ስታንዳርድ የተገነባ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል ነው።
በግንባታው ሂደት ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ማድረጉን አንስተው÷ የመዋኛ ገንዳው ለውኃ ዋና ስፖርት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርና እንደ ሀገር መሰል መዋኛ ገንዳዎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አካዳሚ ዲን ወንድማገኝ ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል መዋኛ ገንዳ መገንባቱ የስፖርት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ያለውን ስራ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
መዋኛ ገንዳው በአንድ ጊዜ ስምንት ተወዳዳሪዎችን ማስተናገድ የሚችል እና በኦሎምፒክ ስታንዳርድ ቁመት እና ስፋት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
የመዋኛ ገንዳው በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል ላይ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተስፋሁን ከበደ