አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራፊክ አደጋ በዓመት ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ነው አለ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር።
በኦሮሚያ ክልል የትራፊክ አደጋ መከላከል ቀን በዛሬው ዕለት በሻሸመኔ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን እንዳሉት÷ የትራፊክ አደጋ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን በተለይም የመንገድ መሠረተ ልማትን ለማስተካከል የተወሰደው ርምጃ ብዙ ውጤት እያመጣ ነው።
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም አሁንም ብዙ እንደሚቀር አንስተው÷ የሕዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ፣ የተሽከርካሪን ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ ብዙ እንደሚቀር እና ሁሉም ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ አቶ ላቺሳ ሀዩ በበኩላቸው÷ በክልሉ በየዓመቱ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እንደሚያጡ አመልክተዋል።
የትራፊክ አደጋ ከሚከሰትባቸው መንስኤዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ በጥንቃቄ ጉድለት የሚመነጭ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የትራፊክ አደጋን መግታት የሚቻለው የፍሰት ተቆጣጣሪዎች በሚያደርጉት ጥረት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሕብረተሰብ ጉዳዩን በባለቤትነት ወስዶ መስራት ሲችል ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደረጄ ባይሳ ናቸው።
በጥላሁን ይልማ