የሀገር ውስጥ ዜና

የሸበሌ ሪዞርት ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ክልል ልማት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

January 31, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሸበሌ ሪዞርት ኢትዮጵያ ውስጥ በትኩረት ከተሰራ በሁሉም ክልል ልማት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው አሉ።

ከ’ገበታ ለትውልድ’ ዐቢይ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለተኛው እና በ385 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው የሸበሌ ሪዞርት በዛሬው ዕለት ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የሸበሌ ሪዞርት ማንም ሰው ልማትና ሰላም ይዞ እስከመጣ ድረስ እንደ ልጅ የመቀበል ባህል መኖሩን በድጋሚ ያረጋገጥንበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ሪዞርቱ ያካተታቸው ቤቶች ግንባታ የአካባቢውን ባህል እና የቤት አሰራር መሰረት ያደረጉ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በሺህ የሚቆጠሩ ዛፎች እና ፍራፍሬዎች የተተከሉበት ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተዋል።

ሰላም ወዳዱ የሶማሌ ሕዝብ ሰዎችን በፍቅር በመቀበል እና በመንከባከብ አብሮነትን በተግባር የሚያሳይ ነው ሲሉም አውስተዋል።

ከዚህ ቀደም ሶማሌ ክልል በግጭትና ጦርነት ይታወቅ ነበር፤ አመራሮችም ወደ ክልሉ የሚሄዱት ለማስታረቅ እና ሰላም ማስከበር እንደሆነ አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን በክልሉ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ሥራዎችና ሌሎች ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አጽንኦት የሰጡት፡፡

ለአብነትም በቅርቡ የተጀመሩት የጋዝ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች፣ በሺህ ኪሎ ሜትር የሚቆጠሩ መንገዶች፣ የቤት ግንባታዎች እና የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን አንስተዋል፡፡

እንዲሁም ዛሬ የተመረቀው የሸበሌ ሪዞርት፣ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች ያሉበት ክልል ሆኖ ወጣቶች በታላቅ ተስፋ መሪዎቻቸውን በደስታ ሲቀበሉ ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

ዕለቱ ሰላም እንደ ዝናብ በሶማሌ ምድር ሲዘንብ ያየንበት ታላቅ ዕለት ነው፤ የክልሉ አመራሮች ክልሉን ከነበረበት ግጭት ወደ ልማት በመቀየራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

በሶስና አለማየሁ