አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አይሻ -2 የንፋስ ሀይል ማመንጫ ፕሮጄክት ለተረጋጋ የኃይል አቅርቦት እና ለቴክኖሎጂ-መራሽ ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ በዛሬው ዕለት ታሪካዊ የሆነውን የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በይፋ መርቀን ለአገልግሎት አብቅተናል ብለዋል፡፡
በሶማሌ ክልል የሚገኘው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የኃይል ዋስትና የማረጋገጥ ስትራቴጂያችን አንድ የማዕዘን ድንጋይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ዓመታዊ ኃይል የማመንጨት አቅሙ 467 ጊጋ ዋት በሰዓት ሲሆን÷ ዘመናዊ የSCADA እና SVG ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለተረጋጋ የኃይል አቅርቦትና ለቴክኖሎጂ መራሽ ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫዎት ተናግረዋል፡፡
የአይሻ ስትራቴጂያዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የንፋስ ኮሪደርነቱ ያለፈ ጠቀሜታ አስገኝቶለታል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ፕሮጀክቱ ለጎረቤት ሀገራት ያለው ቅርበት ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ንግድ ማዕከል ለማድረግ ለተቀመጠው ግብ መሳካት በተግባር የተረጋገጠ ትልቅ እመርታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመደመር መርሕ የኢትዮጵያን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ ወደ የጋራ ሐብት በመለወጥ የአፍሪካ ቀንድን በአካል እና በኢኮኖሚ ይበልጥ ለማስተሳሰር መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡