አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በ21ኛው ሩብ ክፍለ ዘመን የኢኮኖሚ እድገትን የሚያረጋግጡ መሰረቶችን እየገነባች ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
አይሻ-2 የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሸክ ሞሃሙድ በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ለማረጋገጥ ያለመው የብልጽግና ጉዞ የዓለም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ ለምዕራቡ ያደላ እንደነበር አስታውሰው ÷ከምዕራቡ ዓለም ውጭ የነበረው የዓለም ሕዝብ ውስን የኢኮኖሚ እድገት እንደነበረው ጠቅሰዋል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም ቅርፅ እና የዓለም ተቋማት የተገነቡት በጦርነቱ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸውን ሀገራት መልሶ ለመገንባት እንጂ የተቀረው ዓለም ከግምት ያስገቡ ባለመሆናቸው ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ሁሉን አካታች የሆነ አዲስ የኢኮኖሚ ምልከታ እና አዲስ የዓለም እድገት እሳቤን ይዞ መምጣቱን ነው ያስገነዘቡት፡፡
የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው ምዕራፍ የምዕራባውያንን የእድገት ጫፍ እንዲሁም ሁለተኛው ሩብ ክፍለ ዘመን የእስያ ሀገራትን የእድገት ጫፍ አሳይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ 3ኛው እና 4ኛው ሩብ ክፍለ ዘመን ደግሞ የአፍሪካውያን እድገት የሚታይበት እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡
በአፍሪካ ያሉ ወጣቶች አሁን ያለውን ቨርቹዋል ዓለም በትክክል አንብበው መጠቀም ከቻሉ÷ ለመስራት፣ለመፍጠር እና የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ከፍተኛ እድል እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡
በ21ኛው ሩብ ክፍለ ዘመን ጥሩ የኢኮኖሚ ዝግጀት እና መሰረት የጣሉ የአፍሪካ ሀገራት በሶስተኛው እና በአራተኛው ሩብ ክፍለ ዘመን በዓለም ከፍተኛ እድገት ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ እድል አላቸው ነው ያሉት፡፡
ይህ እድል በልጆቻችን መታየት እንዲችል የእድገት መሰረቶችን በመለየት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው ÷ መንግሥትም በሕጻናት ትምህርት እና መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ