የሀገር ውስጥ ዜና

በፈረስ ትርዒት ታጅቦ በድምቀት የተከበረው 86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል…

By Mikias Ayele

January 31, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል “የአብሮነት ቅርስ፤ የሰላም ውርስ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

የአገው ፈረሰኞች ማህብር በጣልያን ወረራ ወቅት የጣልያንን ከኢትዮጵያ መውጣት ተከትሎ በ1932 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነው የተመሰረተው፡፡

የአገው ፈረሰኞች በዓል በጣልያን ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር የተዋደቁ ጀግኖች አርበኞችንና ፈረሶቻቸውን ለመዘከር ታስቦ የሚዘጋጅ ነው፡፡

በየዓመቱ ጥር 23 የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ለ86ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጂባራ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡

በበዓሉ የፈረስ ሠላምታ፣ የድንግል አንሳ፣ የፈረስ ጉግስ፣ የፈረስ ስግሪያ እንዲሁም የሽምጥ ግልቢያ፣ የሴቶችና የዓይነስውራን የፈረስ ትርዒት ተከናውኗል፡፡

በዚህ ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት÷ የአገው ሕዝብና ፈረስ ለዘመናት የዘለቀ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል ዝግጅት ማሳያ ነው።

የአገው ሕዝብ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የሚኖር፣ ለሰላም የላቀ ዋጋ የሚሰጥና በታታሪነቱ የሚታወቅ የዘርፈ ብዙ እሴት ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል።

ዞኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጽንፈኝነትንና ጥላቻን በጽናት በመታገል ለሰላም መስፈን አስተዋፅኦ አበርክቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ÷ዞኑ የሚታወቅባቸው እሴቶችና መልካም ተግባራት ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በበዓሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።