አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት 999 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
አይሻ-2 የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሸክ ሞሃሙድ በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ የሚቀጥለው የአፍሪካ ዘመን መሰረት የሚጣለው ከሞላ ጎደል በታዳሽ ኃይል ኢነርጂ መሆን አለበት ብላ ታምናለች ብለዋል፡፡
መንግሥት የግብርና ዘርፍን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ባከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል፡፡
በተያዘው 2018 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራትም 999 ሚሊየን ኩንታል ምርት ማምረት መቻሉን ጠቁመው ÷ አፈጻጸሙ ከዓመቱ እቅድ 78 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማ ማዘመን፣ በማዕድን ልማት፣ በኢንዱስትሪና ቱሪዝም ከሚገኙ ውጤቶች ባለፈ በመሰረት ልማት እና በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የታዳሽ ሃይል ሥራዎች እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያሰጡ በመሆኑ የኮፕ-32 ጉባዔ በኢትዮጵያ ምድር እንዲዘጋጅ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡
የኮፕ-32 ጉባዔን ኢትዮጵያን፣ አፍሪካን በተለይም ጅቡቲን፣ ሶማሊያን፣ ኬንያን እና ደቡብ ሱዳንን በሚያኮራና በሚያስመሰግን መልኩ ለማዘጋጀት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሸክ ሞሃሙድ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በመገኘት የደስታችን ተካፋይ በመሆናችሁ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
አይሻ-2 የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የጋራ ፕሮጀክት ነው፤ ማስመረቅ ብቻ ሳይሆን ከኢነርጂውም በጋራ የምንጠቀም መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የታዳሽ ኃይል አማራጮቻችንን በስፋት በማሳደግ የሀገሪቱን እያንዳንዱን ማዕዘን እያበራን እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህ ጮራ የጎዳናዎችን ብርሃን ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ተስፋ እና ነገም ጭምር ያበራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ