የሀገር ውስጥ ዜና

በየአካባቢው ያለውን ሃብት በመግለጥ የሚከናወኑ ስራዎች ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ናቸው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

By abel neway

February 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) መንግሥት በየአካባቢው ያለውን ሃብት በመግለጥ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ናቸው አሉ።

ከ’ገበታ ለትውልድ’ ዐቢይ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለተኛው እና በ385 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው የሸበሌ ሪዞርት ትናንት መመረቁ ይታወሳል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የግንባታ ፕሮጀክቱ አስተባባሪ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት÷ የሸበሌ ሪዞርት 46 ሺህ ስኩዌር ሜትር የሚሸፍን የመልክዓ ምድር ማስዋብ ስራ የተሰራለት ነው፡፡

ሪዞርቱ የእንግዳ መቀበያ ማዕከል፣ ሱቆች፣ ባህላዊና ዘመናዊ ምግብ ቤቶች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች እና አንፊ ቲያትሮች ተካተውበት ተገንብቷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም 150 ሰው የሚይዝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ስፓ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የውበት ሳሎን፣ ሶስት መዋኛ ገንዳዎች እንዲሁም የህጻናት መጫወቻ ስፍራ እንዳሉት ገልጸዋል።

የሱማሊ ህዝብ የኑሮ ዘዬና አኗኗርን የሚያሳዩ ባህላዊ ግንባታዎች እና የህንጻ ዲዛይኖች ታሳቢ ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡

የፕሮጀክቱ አካባቢ አረንጓዴና በሂደትም ጫካ ለማድረግ በማቀድ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ150 ሄክታር በላይ የሚሸፍኑ 360 ሺህ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን አብራርተዋል።

በዚህም የፍራፍሬዎች ፓርክ እንዲኖሩት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ምቹ የሆኑ 24 መኖሪያ ቤቶች በመገንባትና የቤት ቁሳቁስ በማሟላት ፕሮጀክቱ በሚገኝበት አካባቢ በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ዜጎች የማስረከብ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

የሸበሌ ሪዞርትን ጨምሮ መንግሥት በየአካባቢው ያለውን ሃብት በመግለጥ የሚያከናውናቸው ስራዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ናቸው ያሉት አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፤ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር በቀጣይ ለተሻለ ውጤት መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ሸበሌ ወረዳ የተገነባው የሸበሌ ሪዞርት ፕሮጀክት በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ 15 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ የእግረኛ መንገዶችን ይዟል።

በአቤል ነዋይ