የሀገር ውስጥ ዜና

ተቋማት ሀገርን ታሳቢ ባደረገ ከፍታና ቅንጅት መስራት አለባቸው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Adimasu Aragawu

February 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ተቋማት ሀገርን ታሳቢ ባደረገ ከፍታ እና ቅንጅት መስራት አለባቸው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ 14 ተቋማት የ2018 በጀት ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ዛሬ በተገመገመበት ወቅት ነው፡፡

በዓመታት አንድ ሁነኛ ፕሮጀክት መፈጸም ብርቅ በሆነባት አፍሪካ ኢትዮጵያ በየንጋቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየመረቀች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

የለውጡ መንግሥት “መንገዳችን መደመር መዳረሻችን ብልጽግና” በሚል እንደ ዐለት በጸና አቋሙ በልዩ የመንግሥትነት እሳቤ እና አመራር በጽናት፣ በእውቀት እና በድፍረት በመስራት የኢትዮጵያን የልማት እና ብልጽግና ታሪክ አድምቆ እየጻፈ ነው ብለዋል፡፡

ከሕዝብ በምርጫ ካርድ የወሰድነውን ኮንትራት በታላቅ ትጋት እና የሀገር ፍቅር መንፈስ እየተገበርን ነው በማለት ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከማጠናቀቅ በተጨማሪ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም ታላላቅ ሀገራዊ የነዳጅና ማዳበሪያ ፕሮጀክቶች በሶማሌ ክልል እና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መጀመራቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ሸበሌ ሪዞርትን ከወዳጅ ጎረቤት ሀገራት ጋር ሆነን አስመርቀናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ወንጪ፣ ጨበራ፣ ጎርጎራ፣ ቤኑና እና ሌሎች ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክቶች በለውጡ መንግሥት መገንባታቸውን አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታትም ሆነ በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ባስመዘገብነው ድል እየተበረታታን ለቀጣይ ለተሻለ ውጤትና ድል እንዘጋጃለን ነው ያሉት፡፡

በዚህም ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም ሞዴል የሆነ ስራ እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

በለይኩን ዓለም