አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ተነጣጥለው መኖር አይችሉም አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ነው ይህንን ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ቀይ ባሕርን ለመጠቀም ሰው ልግደል አላለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በውውይትና በስምምነት እንዲሁም በገበያ ህግ በድርድር ጉዳዩን እንፍታው ነው ያልነው ብለዋል።
እኛም ማጋራት አለብን እነሱም ማገዝ አለባቸው፤ ኢትዮጵያን ጎድቶ ትርፋማ መሆን አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር አያስፈልጋትም ብሎ የሚያስብ ሰው አንድ ተፈጥሯዊ ህግ የሳተ ነው፤ ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘለዓለሙ ተነጣጥለው መኖር አይችሉም በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ እንዳይቀደድ የተሰፋ እንዳይጣመር የተቀፈደደ ከባቢ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ በባህልና ቀንቋ የሚተሳሰሩ ሕዝቦች ያሉበት ቢሆንም ከፍተኛ ፉክክርና ጣልቃ ገብነት ያለው ከባቢ ነው ብለዋል።
የሁለቱ ውሃዎች ጉዳይ እኛንም እያተረማመሰ በእኛ ጉዳይ የሚገቡ ሃይሎችን እያሰፋ አንዱ ለአንዱ መከታ ሊሆን ሲገባው ችግር አስተላላፊ ሆነ በማለት ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያትም ቀጣናው የራሱ ችግር ያለበት በመሆኑ ይህን ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፤ እንደሚሳካም እምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል።
ሰሞኑን የጅቡቲ እና የሶማሌው ፕሬዚዳንቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና በተመሳሳይ ባህልና ቋንቋ ከሕዝቡ ጋር መግባባት ችለው እንደነበር አስታውሰዋል።
አንዱ ጎረቤት ጋሻ መሆን ሲገባ ጥይት አቀባባይ ሆኖ ቀረ፤ ይህን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሶስና አለማየሁ