አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ አጠቃቀም 16 በመቶ እድገት አሳይቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያን አምራች ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያም፤ የኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ ሳይጀመር ኢንዱስትሪዎች 47 በመቶ ብቻ ያመርቱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ኢንዱስትሪዎቹ 66 ነጥብ 3 በመቶ ማምረት መቻላቸውን ገልጸው÷ ይህም የአምራች ኢንዱስትሪው እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ከግብርና ውጭ በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ቢዝነሶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ከነዚህ ውስጥ 17 በመቶ የሚሆኑት አምራች ኢንዱስትሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለው የብድር፣ የመሬት አቅርቦት እና የቴክኖሎጂ አቅርቦት እድገት እያሳየ መሆኑን እና በዚህ 6 ወር ውስጥ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ አጠቃቀም ብቻ 16 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ምሳሌ የሚሆኑ ኢንቨስተሮችን እየሳበ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ አቅም እያሳደጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ከቬትናም በመጡ ባለሀበቶች የሚመራው የቶዮ የሶላር ኩባንያ ባለፉት 6 ወራት ብቻ 66 ሚሊየን ዶላር ግምት ያለው ምርት ወደ ውጭ መላኩን ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ ወደ አምስት የሚጠጉ በሶላር ኢነርጅ ዘርፍ የሚሰሩ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልፀው፤ በቀጣዩ ዓመት ሙሉ በሙሉ ስራ እንደሚጀመሩ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በሚቀጥለው ዓመት ብቻ ከሶላር ምርት 900 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ