አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ስድስት ወራት ከወጪ ምርት የተገኘው 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ከዚህ ቀደም በሙሉ ዓመት እንኳን ተገኝቶ አያውቅም አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ለውጪ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ለማግኘት የታቀደው 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፥ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት የዕቅዱን 120 በመቶ አሳክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ ገቢ ከዚህ ቀደም በሙሉ ዓመት እንኳን ተገኝቶም ታቅዶም እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡
በዚህ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከአገልግሎት ወጪ ንግድ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰው፥ በዚህም 17 በመቶ እድገት ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡
ከሀዋላ 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንና ይህም 39 በመቶ እድገት እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገደማ የተገኘበት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 20 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
ርዳታና ጤነኛ ብድሮችን ከመሳሰሉ ሌሎች የገቢ ምንጮች ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ የተገኘ ሲሆን፥ ባለፉት ስድስት ወራት በተገኘው ገቢና ምርት ከውጪ ለማስገባት ባወጣነው ወጪ መካከል አዎንታዊ ውጤት መታየቱን አብራርተዋል፡፡
ምርት ከውጪ ለማስገባት ወጪ ከተደረገው 11 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ውስጥ 39 በመቶው ምርት ለማምረት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ለመግዛት መዋሉን ጠቅሰው፥ ይህም ወጪያችን ጤናማ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም እናስገባ የነበረውን በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻላችን የምናስገባውን ምርት በመቀነስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ማዳን ችለናል ነው ያሉት፡፡
በሶስና አለማየሁ