የሀገር ውስጥ ዜና

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነፃፀር በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ አሁንም ዝቅተኛ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

February 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነፃፀር በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ አሁንም ዝቅተኛ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ነው ይህንን የገለጹት፡፡

በተለያዩ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጉዳዮች ምክንያት ባለፈው ዓመት ነዳጅ የዋጋ መዋዠቅ ሲያሳይ እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ላይ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት አንጻር ሲታይ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም ከውጪ ተገዝቶና ወደብ ሳይኖረን በድጎማ ኃይል ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ባነሰ ዋጋ ነዳጅ እያቀረብን እንገኛል ብለዋል።

ነዳጅ የሚጠቀሙ ትራተሮችና የውሃ ፓምፖች እየጨመሩ በመምጣታቸው ከዚህ ቀደም ከምናወጣው የሚበልጥ ወጪ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚታዩ ችግሮች ዋነኛ መንስኤ ስግብግብ የሆኑ ሰዎች ከዚህ ድጎማ ለመቀራመት የሚያደርጉትን ጥረት በበቂ ሁኔታ መቆጣጠር አለመቻል እንደሆነም ጠቁመዋል።

በዚህም ዘመናዊ የክትትል ስራ እየተሰራ እንደሆነና የእያንዳንዱን ነዳጅ ጫኝ ቦቴ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ብሎም ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ በእያንዳንዱ የነዳጅ ማደያ የቁጥጥር ስራዎችን ለመስራት እየተሞከረ መሆኑን አብራርተዋል።

በአጠቃላይ በድጎማ፣ ገቢን በማሳደግ፣ በግብይት ሰንሰለት፣ በመብራት እና ነዳጅ ዋጋ የተሰራው ስራ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ተችሏልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው።

አሁንም የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ዋና ዋና ጉዳዮች በሆኑት በምግብ፣ ቤት፣ ትራንስፖርት፣ ትምህርት ቤት ምገባ እና ገቢን በማሻሻል ረገድ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዮናስ ጌትነት