አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ቀየረ፡፡
የፌደራል ፖሊስ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ ፊጣ÷ ከ50 ዓመታት በላይ አገልግሎት ላይ የነበረው የፌደራል ፖሊስ ተሽከርካሪ ሰሌዳ የተዘበራረቀና ወጥነት የሌለው እንዲሁም ለቁጥጥር አመቺ እንዳልነበር ተናግረዋል።
በንጽጽር አዲሱ የተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ እና ከመረጃ ቋት ጋር የተጣመረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰሌዳው በህገወጥ መንገድ የማይባዛ ሚስጥራዊ መለያዎችን የያዘ መሆኑ ለቁጥጥር እንዲሁም የስራ እንቅስቃሴን ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የተሽከርካሪ ሰሌዳው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከማላቅ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸው÷ ለሕዝቡ የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም የወንጀል ምርመራና ክትትል ስራን ለማሳለጥ አጋዥ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል 2030 ግብ ከማሳካትና አገልግሎቶችን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ትልም ጋር የተዛመደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሔብሮን ዋልታው