አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር ህዝባዊነትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በህዝቦች መካከል የዘለቁ ችግሮች ተፈትተው የጋራ ትርክት ለመገንባት ያስችላል አሉ ምሁራን።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና ስነ ልማት ጥናት መምህር ፍቃዱ ቶሎሳ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ በህዝቦች መካከል የነበሩ ቅራኔዎችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል አካታች መድረክ ሳይፈጠር ቆይቷል።
በዚህም በህዝቦች መካከል የዘለቁ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል ዕድል እንዳልነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ሁሉም አጀንዳውን በማቅረብ በምክክር ለመፍታት የሚችልበት ሂደት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
አሳታፊና አካታች ሀገራዊ ምክክር በህዝቦች መካከል የዘለቁ ችግሮችን በመፍታት ለጋራ ትርክት መሰረት ይጥላል ያሉት ፍቃዱ ቶሎሳ (ዶ/ር)፤ የጋራ ትርክት ለሀገረ መንግስት ግንባታ የጎላ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በምክክር እና በውይይት ለችግሮች መፍትሔ ማበጀት የሰለጠነ የፖለቲካ ምህዳር ውጤት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙላለም ኃይለማሪያም በበኩላቸው፤ ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በውይይት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ለሀገረ መንግስት ግንባታው የላቀ ሚና እንደሚወጣ አውስተዋል።
ዜጎች በሀገር ጉዳይ ያገባኛል በሚል መንፈስ እንዲነጋገሩ አውድ መፈጠሩ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች መተማመን እንዲፈጠር እና የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር እያስቻለ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ናቸው።
ኮሚሽነሩ ባለፉት አመታት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ህዝቡን የሚወክሉ አካላትን በመምረጥ እና አጀንዳዎችን በመለየት ዘላቂ ለሆነ ሀገረ መንግስት ግንባታ ትርጉም ያላቸው ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
በወርቅአፈራው ያለው