የሀገር ውስጥ ዜና

የኢኮኖሚ ማሻሻያው አመቺ የንግድ ከባቢ እንዲፈጠር አስችሏል – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

By Adimasu Aragawu

February 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ የንግድ ማህበረሰብ አመቺ የንግድ ከባቢ እንዲፈጠር አስችሏል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።

15ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት “የኢትዮጵያን ይግዙ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፥ መሰል የንግድ ትርኢቶች የወጪ ንግድን ለማሳደግና የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያዎች ለማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።

በተጨማሪም የንግድ ፖሊሲዎችን ወደ ተግባር ለመቀየርና ሻጮችን፣ ሸማቾችንና ኢንቨስተሮችን ለማገናኘት ትልቅ እድል ይፈጥራሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የተገበረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ውጤቶችን እያስገኘ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።

ማሻሻያው ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለውጪው የንግድ ማህበረሰብ አመቺ የንግድ ከባቢ እንዲፈጠር አስችሏል ብለዋል።

መንግሥት ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው÷ በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማብቃት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው÷ ም/ቤቱ የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የንግድ ትርዒቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ ለአምራቾች የገበያ እድል ለመፍጠርና በሀገር ውስጥና በውጭ አምራቾች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ትብብር በተዘጋጀው የንግድ ትርዒት ላይ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።

የንግድ ትርዒቱ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ቀናት እንደሚካሄድም ተገልጿል።

በኃይለማሪያም ተገኝ