የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በበጋ መስኖ ልማት ከ318 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል

By Mikias Ayele

February 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በክልሉ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት ከ318 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል አለ፡፡

በቢሮው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አንተነህ ሰውአገኝ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ክልሉ ዘንድሮ 502 ሺህ 813 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት አቅዷል።

ከዚህ ውስጥ 331 ሺህ 905 ሄክታሩ ነባር ሲሆን 170 ሺህ 908 ሄክታሩ አዲስ መሬት መሆኑን ተናግረዋል።

በመስኖ ከሚለማው መሬት 350 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል እንደሚሸፈን ጠቅሰው፤ ከዚህም 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት።

አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶች ተደራሽ እየሆኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ እስካሁን 544 ሺህ 540 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 457 ሺህ 339 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ከ63 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።

የአርሶ አደሩ የውሀ አጠቃቀም ልምድ እየተሻሻለ በመምጣቱ የመስኖ ልማት ውጤታማነት ማደጉን ገልጸዋል።

ከስንዴ በተጨማሪ ቲማቲም፣ ድንች፣ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ቀይስር የመሳሰሉ አትክልቶች በተለያዩ አካባቢዎች በመስኖ አማካኝነት በስፋት እየለሙ መሆኑን አመልክተዋል።

በሚኪያስ አየለ