ቢዝነስ

ኢትዮ ቴሌኮም ከጅቡቲ እና ሱዳን የቴሌኮም ኩባንያዎች ጋር በትብብር ለመስራት ተስማማ

By Yonas Getnet

February 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ግሩፕ የሆራይዘን ድንበር ተሻጋሪ የፋይበር መስመር ዝርጋታን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት በዛሬው ዕለት በጅቡቲ ተፈራርመዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የሦስትዮሽ ስምምነቱ የጋራ የዲጂታል ወደፊት ዕጣ ፈንታችንን ለመገንባት የሚያስችል ነው።

የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ጠንካራና ከፍተኛ አቅም ያለው እንዲሁም አፍሪካን በዲጂታል የሚያስተሳስር የኮኔክቲቪቲ ኮሪደር ለመፍጠር የተወሰደ ወሳኝ ርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም የጅቡቲን የባሕር ውስጥ የፋይበር ኬብሎች በኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ከሱዳን ጋር በማስተሳሰር ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን የሚያጠናክር፣ አስተማማኝ የየብስ መስመር ተግባራዊ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ ሀገራትን በትብብር የሚያስተሳስር፣ ኢኮኖሚን የሚያጠናክር እና ለቀጣናውም በዓለም አቀፍ የዲጂታል ምህዳር ውስጥ ጠንካራና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መግቢያ እንደሆነ አንስተዋል።

የጅቡቲ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ አሶዌ ቡህ በበኩላቸው÷ የሆራይዘን ፕሮጀክት ለሀገራቱ የጋራ እድገትና ብልጽግና ያለንን ራዕይ መሰረት በማድረግ በቀጣናው የቴሌኮም መሠረተ ልማትና ትስስር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ስትራቴጂካዊ መሠረተ ልማትን በጋራ የመገንባት አቅምን የሚያሳይና የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማጠናከር በዓለም አቀፍ መድረክ ያለውን ሚና የሚያረጋግጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህ ፕሮጀክት ከመሠረተ ልማት ግንባታነት ባሻገር በአፍሪካ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች መካከል ለሚደረግ የፈጠራ አጋርነት ህያው ምስክር ነው ያሉት ደግሞ የሱዳቴል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማግዲ ሞሀመድ ናቸው።

ፕሮጀክቱ የጋራ ራዕይና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ሲጣጣሙ እንዲሁም ፉክክር በትብብር ሲተካ የሚገኘውን ውጤት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው÷ መላው የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ሊወስዱበት የሚያስችል እንደሆነም አመልክተዋል።

የተፈረመው ስምምነት ከፍተኛ አቅም ያለው ድንበር ተሻጋሪ የኦፕቲካል ፋይበር መሠረተ ልማት ለመዘርጋት እና የቀጣናውን ዲጂታል ትስስር ወደ ላቀና አስተማማኝ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል እንደሆነ ኢትዮ ቴሌኮም ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል።