አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕድን ምርት ሒደት የአካባቢ ጥበቃ ሥራን እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ባከበረ መልኩ እንዲከናወን በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)።
የ12 ሀገራት የማዕድን ዘርፍ ተወካዮች እና የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ተዋናዮች በተገኙበት ዓለም አቀፍ የሲያናይድ ማኔጅመንት ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ጉባዔው ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃ.የተ.የግ.ማ በሲያናይድ አጠቃቀም በ2025 ዓለም አቀፍ የዕውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተከትሎ ነው በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው።
ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፥ የማዕድን ዘርፍ ለሀገር ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በኢትዮጵያ በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም በሚገባ ለመጠቀም በትኩት እየተሰራ ነው።
በተለይም የወርቅ ምርትን ለማሳደግ በተከናወነ የተቀናጀ ሥራ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ነው የገለጹት።
የዘርፉ ዕድገት የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ባከበረ መልኩ እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ መከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ለዚህም የሲያናይድ ኢንስቲትዩትን እውቅና በማግኘት በምርት ሒደት ላይ የሲያናይድ ኬሚካልን መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃ.የተ.የግ.ማ ሲያናይድ ኬሚካልን በምርት ሒደቱ ላይ በመጠቀም እውቅና ማግኘቱን አድንቀው፤ ሌሎች የዘርፉ ኩባንያዎች ተሞክሮውን ሊወስዱ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመላኩ ገድፍ